10. የሀገራችን የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ነባራዊ ሁኔታ

nty

ሰኔ 29, 2023

የውጭ ሀገራት የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ማስከበር ሂደት ከ300 ዓመታት እና ከዛ በፊት ጀምሮ ተግባራዊ አደረጎታል ፡፡ አብዛኛው የአፍሪካ ሀገራትም ከሀገራችን በተሻለ ሁኔታ እየተገበሩት ይገኛሉ፡፡ የቅጅ መብት ኢንዱስትሪ ኢኮኖሚያዊ እድገት ዋልታዎች ተብለው ከሚጠቀሱት ታላላቅ ኢንዱስትሪዎች የሚመደብ ዘርፍ ነው፡፡ ይህ ሴክተር በተለይም በፍጥነት በማደግ ወደር የማይገኝለት ኢንዱስትሪ እንደሆነ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡ የውጪ ምንዛሬ በማስገኘትም ከኬሚካልና ተዛማጅ ምርቶች፣ ከምግብና ከቁም እንሰሳት፣ ከመኪናና ከመኪና መለዋወጫ፣ ከአውሮፕላንና ተያያዥ ጥሬ እቃዎች የበለጠ ነው፡፡

የሀገራችን የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ነባራዊ ሁኔታ

በርካታ ሀገራት የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ህግ እና የዘርፉን ጥቅም በመረዳት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡ ለምሳሌነት ለዘርፉ ከፍተኛ ድጋፍ ከሚያደርጉ ሀገራት ጥቂቶቹን ለመጥቀስ አውስትራሊያ፣ ቤልጂየም፣ ካናዳ፣ ፊንላንድ፣ፈረንሳይ፡ ጀርመን፣ ሉክሰምበርግ፣ ኔዘርላንድስ፣ ስዊዲንና አሜሪካ ይገኙበታል፡፡ የሀገራችንን የኮፒራይት ኢንዱስትሪ ስንመለከት ደግሞ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የተሻሉ የዕድገት ደረጃዎችን እያስመዘገበ የመጣ ዘርፍ ቢሆንም ያሉትን መልካም አቅሞች እና ዕድሎች አሟጦ በመጠቀም ዘርፉን በሚገባ ከማሳደግ አንጻር በርካታ ተግዳሮቶች የተጋረጡበት መሆኑ በተለያየ አጋጣሚ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ጥናቶችን ይህንኑ ያሳያሉ፡፡

ከ1996 ዓ.ም በፊት የዘርፉ ዋነኛ ማነቆ የነበረው የኪነ ጥበብ እና የስነጥበብ ባለሙያዎች በሚሰሯቸው የፈጠራ ስራዎች ላይ ያላቸውን መብት ለማስጠበቅ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ አለመኖር እንደነበርም ግልፅ ነው፡፡ይህ የህግ ችግር ለመቅረፍ በዘርፉ የተደራጁ የባለመብቶች ማህበራት እና በራሳቸው ተነሳሽነት ለመብቶች መከበር ሲታገሉ የነበሩ ጥቂት ግለሰቦች ባደረጉት ጥረት መንግስት የችግሩን አሳሳቢነት እንዲረዳ በማስቻሉ በ1996 ዓ.ም የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 410/96 እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ የአዋጁን መውጣት ተከትሎ የኪነ ጥበብ እና የስነ ጥበብ ስራዎች ከባለመብቶች ፍቃድ ውጪ በሲዲ፣ በቪሲዲ፣በዲቪዲ፤ በፍላሽ፣ በሚሞሪ እና በመሳሰሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በማባዛት እና በኢንተርኔት በማሰራጨት ለዘመናት ህገ ወጥ ተግባር ይፈጽሙ በነበሩ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃዎችን ለመውሰድም ጥረቶች ሲደረጉም ቆይተዋል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎንም ዘርፉ እጅጉን ለዘመኑ ቴክኖሎጂ ተጋላጭ በመሆኑ እና የሚፈጸሙት የመብት ጥሰቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ የተለያየ መልክ የሚይዙ (የተራቀቁ) በመሆናቸው እነዚህን በየጊዜው የሚከሰቱ የመብት ጥሰቶችና ህገ ወጥ ተግባራትን ለመከላከል የሚያስችል አሰራር የሚዘረጋ የህግ ማሻሻያ ለማድረግ መንግስት እና ባለመብቶች በጋራ ባደረጉት ጥረት በ1996 ዓ.ም የወጣው የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 410/1996 በ2007 ዓ.ም በወጣው አዋጅ ቁጥር 872/2007 ማሻሻያ ተደርጎለታል፡፡ ተሻሽሎ የወጣውን ህግ መሠረት በማድረግ ከላይ የተዘረዘሩትን እና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች እንደሚፈታ የታመነበትን "የኢትዮጵያ የቅጅና ተዛማጅ መብቶች የጋራ አስተዳደር ማህበር" ለማቋቋም ህጉ ተሻሽሎ ከወጣበት ቀን ማግስት ጀምሮ በርካታ ጥረቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ይህ ጥረታቸው ተሳክቶ ዘርፉን የሚመራ በመላው ሀገራችን የሚገኙ የዘርፉ 17 ማህበራት እና በዘርፉ የሚንቀሳቀሱ ባለመብቶች በጋራ በመሆን ‹‹የኢትዮጵያ የቅጅና ተዛማጅ መብቶች የጋራ አስተዳደር ማህበር›› በሰኔ 11 ቀን 2009 ዓ.ም ተሻሽሎ በወጣው አዋጅ 872/2007 መሰረት ተቋቁሟል፡፡